@nobel12.21: ቅዱስ ያሬድ ታሪክ (፭፻፭-፭፻፸፩) የቅዱስ ያሬድ የስሙ ትርጉም ያሬድ፦ማለት ርደት፣ወሪድ ማለትም መውረድ ማለት ነው።ከአዳም ስድስተኛው በሆነው በመላልኤል ልጅ በያሬድ ጊዜ ደቂቀ ሴት ከደብር ቅዱስ ወደ ደቂቀ ቃየን ወደ ምድረ ፍዳ ስለወረዱ ያንን ለማስታወስ አባቱ መላልኤል ያሬድ ብሎታል።በኢትዮጵያም ዳግማዊው ያሬድ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተነሥቶ ሰማያዊውን ልዩ ጣዕመ ዜማ ወደ ኢትዮጵያ የሚያወርድ ነውና ይህን ለመግለጽ እግዚአብሔር በእናት አባቱ ላይ አድሮ ያሬድ እንዲባል አድርጓል። ያሬድ፦ማለት ንብ ማለት ነው።ንብ የማይቀምሰው አበባ እንደሌለ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም በቅዱሳት መጽሐፍት የማይተክሰው የለም። ያሬድ፦ማለት ረአዬ ምስጢር፣ ነጻሬ ኅቡአት “ምስጢር ተመልካች፣ምስጢር ገላጭ መባሉ የመላእክት ምስጢራት ጸዋትወ ዜማ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯልና ከቅዱሳን መላእክት በሰማይ የሰማሁት ዜማ ምን ይረቅ ምን ይጠልቅ ስላለ ረአዬ ምስጢር ተብሏል።ነጻሬ ኅቡአት መባሉ ደግሞ ስውር የሆነ የጻድቃንን፣የሰማዕታትን፣የነቢያትንና የሐዋርያትን ገድል አስፍቶ ስለ ሚናገር ነው። የቅዱስ ያሬድ አስተዳደግ ቅዱስ ያሬድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ትውልዱ አክሱም ነው።ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም ከእናቱ ክርስቲና(ታውክልያ)ና ከአባቱ ይስሐቅ(አብዩድ) ተወለደ።አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር።በዚያን ጊዜ የብሉያትና የሐዲሳት መምህራንና ተማሪዎች የሚገኙበት አክሱም ጽዮን ነውና የአክሱም ቤተ ጉባኤ መምህር የነበረው እናቱ ወንድም ጌዴዎን ነበር።የሰባት ዓመት ብላቴና በሆነ ጊዜ አባቱ ስለ ሞተ ከአጎቱ ዘንድ ሊማር ሔደ።ኾኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለ ነበረ አብረው የሚማሩት ህጻናት ይቀልዱበት ነበር።አጎቱ ጌዴዎንም ከሕጻናቱ ጋር ሊወዳደር ባለመቻሉ በጨንገር በአለንጋ ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር መደባይ ሲጓዝ የኢትዮጵዊቷ ንግስተ ሳባና የእስራኤል ንጉስ የሰሎሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ የተቀበረበት ቦት ደረሰ።ለጥሙ ከምንጭ ውኃ ጠጥቶ ለድካሙ ከዛፉ ጥላ አረፈ።ይኸውም ክሬዋሕ በሚባል ዛፍ ሥር በውኃው ምንጭ ዳር ሥር ተቀምቶ አንድ ትል የዛፏን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ እየወጣ እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኃላ በሰባተኛው ጊዜ ወደ ዛፉ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ ተመልክቷል።ያሬድም ከዚህ ትል ትዕግሥትን፣ጽናትን፣ጥረትን፣ ስኬትን ተምሮ ወደ መምህሩ ጌዴዎን ተመልሷል እግዚአብሔርም ልብናውን በመመልከት ዕውቀትን ገልጾለታል።ቅዱስ ያሬድም ውዳሴ ማርያምን፣መዝሙረ ዳዊት፣ነቢያት፣መሐልየ ሰሎሞን፣ብሉያትና ሐዲሳት ተገልጾለታል። ለቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ መገለጥ ኅዳር 5 ቀን 527 ዓ.ም ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት እግዚአብሔር ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን እርሱ ወዳለበት ላከ እነርሱም ያሬድ ባለበት ቦታ አንጻር በአየር ላይ ረብበው በግእዝ ቋንቋ "ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ (የተመሰገንክና የተባረክ ያሬድ ሆይ፤ አንተን የተሸከመች ማሕፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው)"ብለው አወደሱት። ቅዱስ ያሬድም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ አንጋጦ ሦስቱን አዕዋፍ አየና "እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ከወዴት መጣችኹ" አላቸው። ከሦስቱ አዕዋፍ አንዷም "ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ማሕሌትን ሰምተኽ እንድታዜም የተመረጥኽ መኾኑን እነግርህና እናበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልከን መጥተናል አለችው። ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ። በዚያም ቅዱሳን መላእክት የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ እግዚአብሔር በቅኔና በከፍተኛ ደምፅ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ኾነው ሲያመሰግኑ እንዲሁም የእንዚራ፣ የበገና የመሰንቆ ድምፅ በሰማ ጊዜ ካለበት ሥፍራ እነርሱ ወዳሉበት ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም። በመጨረሻም እነዚያ አዕዋፍ ወደ እርሱ ተመልሰው መጡ። "ያሬድ ሆይ፤ የሰማኸውን አስተውለኸዋል?" ብለው ጠየቁት እርሱም "አላስተዋልኸም" ብሎ መለሰላቸው። እንግዲያውስ አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ጥራ፤ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ከእግዚአብሔር መዘምራን ከቅዱሳን መላእክት በየዐይነቱ ዜማ ያለውን ማሕሌት ትማራለኽ፤ ታጠናለኽ" አሉት። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ማሕሌቱን በየዓይነቱ አውጥቶ "መልካምን ነገር ልቤ ተናገረ" እያለ ከቅዱሳን መላእክት ተማረ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም "ሌሎችን አገልጋዮች ሰዎች ይሾሟቸዋል፤ አንተን ግን እኔ ሢመተ ክህነት (ቅስና) ሾሜኻለሁ" አለው። ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዓታቸው ዐይቶ፤ ማሕሌታቸውን አጥንቶ ኅዳር 6 ቀን 527 ዓ.ም በጠዋት ሦስት ሰዓት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል። ከዚያም ኾኖ ፊቱን ታቦተ ጽዮን ወዳለችበት ወደ ምሥራቅ አዙሮ እጆቹን ዘርግቶ እንዲህ ብሎ ሰማያዊ ዜማን ለመጀመርያ ጊዜ በአኵሱም አደባባይ (ዐውደ ምሕረት) ዘመረ። “ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብር ግብራ ለደብተራ"። ብሎ በዓራራይ ዜማ አዜመ። ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር አሁንም ላለ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው። ስለምን በዓራራይ ዜማ ጀመረ ቢሉ ቋንቋን የሚያናግር ምስጢር የሚያስተረጉም መንፈስ ቅዱስ የገለጠልኝ ዜማ ነው ሲል ነው። ምክንያቱም ዓራራይ ዜማ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነውና። በመጨረሻ ቅዱስ ያሬድ ካህን ዘመኑን ሁሉ በመላእክት ማኅሌት እግዚአብሔርን በማገልገልና ይህን ማኅሌት ለሚከተሉት ደቀ መዛሙርት በማስተማር ዘመኑን ፈጽሞ ለሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በምናኔ ታግሦ በገድሉና በጣዕመ ዜማው ፀላኤ ሠናያትን ድል አድርጎ ከዚህ ዓለም ድካምና መከራ የሚያርፍበት፣ የሚሰወርበት ቀንና ሰዓት መድረሱን በጸጋ በዐወቀ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ "ይቤ ጳውሎስ ኃላፊ ንብረቱ ለዝንቱ ዓለም አኃውየ አስተፋጥኑ ገቢረ ሠናየ አነሰ በድረየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሠለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየዓሥየኒ መኰንነ ጽድቅ" 2ጢሞ4፥7-8 እያለ በሚያራራ ቃል ምክሩን ሰጥቶ ተሰናበታቸው። እነርሱም ምክሩን ተቀብለው "አባ አቡነ፣ አባ መምህርነ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተኀድገነ፤ አባታችን መምህራችን ወደ የት ትሔዳለኽ? ለማንስ ትተወናለኽ? እያሉ ሲያዝኑ ሲያለቅሱ በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ግንቦት11 ቀን በ571ዓ.ም ተሰወረ። ቅዱስ ያሬድ ከመሰወሩ በፊት በእግዚአብሔር አምነው በእርሱ ቃል ኪዳን ለተማፀኑ፣ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ላሳነጹና ላነጹ፣ መጽሐፈ ገድሉን ለጻፈና ላጻፈ፣ ዕጣን ቋጥረው ጧፋና ጥላ ገዝተው መገብሪያ ሰፍረው፣ መጋረጃና ሌሎችንም ንዋያተ ቅዱሳት ገዝተው አምጥተው በስሙ ለታነጹ አብያተ ክርስቲያናት ላበረከቱት ሁሉ የማያልፈውን ርስት መንግሥተ ሰማያት እንደሚያወርስለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ገብቶለታል። #fyp #viral #foryou

Nobel
Nobel
Open In TikTok:
Region: ET
Sunday 18 May 2025 15:29:20 GMT
7921
555
4
183

Music

Download

Comments

mehrtab21
ሊንጊኖስ :
🥰🥰🥰
2025-06-12 17:24:39
1
betselot_as
በጸሎተ ሚካኤል :
😍😍😍😍
2025-06-06 09:44:28
1
buraman480
ሠራዊተ ሚካኤል :
🥰🥰🥰
2025-05-19 07:47:44
1
haylemelekot12
ሜሎስ :
❤️
2025-05-18 16:46:17
1
To see more videos from user @nobel12.21, please go to the Tikwm homepage.

Other Videos


About